ወጣቱ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ሊያስቀጥል ይገባል-አቶ ደሴ ዳልኬ

የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ወጣቱ የራሱን ሚና ተረድቶ በተደራጀ አግባብ መንቀሳቀስ እንዳለበት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛው ዓመት ምክንያት በማድረግ "አዲሲቷ ኢትዮጵያና የወጣቱ ሚና" በሚል መሪ ቃል ትናንት በሀዋሳ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤የረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞዋን ለማሳካት የወጣቱ ሚና የጎላ ነው፡፡

"አገሪቱ ከድህነት ለመላቀቅ የጀመረችው የሕዳሴ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆንም ወጣቱ ጠንካራ ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡

ትግሉ ወጤታማ እንዲሆንም ወጣቱ ከምንጊዜም በላቀ መልኩ አደረጃጀቱን በማጠናከር  የሕዳሴው ታሪክ ሰሪና ባለቤት መሆኑን ማሳየት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

አስከፊውን የንጉሳዊ ስርዓትና አምባገነኑን ደርግ ለመጣል ለዓመታት በተከናወኑ እልህ አስጨራሽ ትግሎች ውስጥ ወጣቱ ሕይወቱን በመሰዋት ታላቅ ተጋድሎ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ይህን ተጋድሎ የፈጸሙ ወጣቶች ዛሬ በሕዳሴ ጉዞ ላይ ያለች አገር አስረክበውናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  ለነገው ትውልድ የሚሆን ታሪክ ሰርቶ ማለፍ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ በበኩላቸው "ወጣቱ ያለፈውን ትውልድ ታሪክ ጥላሸት ለማልበስና እየተገነባች ያለችውን አገር ለማፍረስ የሚደረግን ማናቸውንም ጥቃት በመመከት የተረከበውን አደራ በብቃት የመወጣት ኃላፊነት አለበት" ብለዋል፡፡ 

ውድ ታጋዮች በከፈሉት መስዋዕትነት የዛሬው ትውልድ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወጣቱ ዛሬ የተገኘውን ሰላምና ልማት ጠብቆ በማስቀጠል ለተተኪው ትውልድ ተስፋ የምትሆን አገር ማስረከብ እንዳለበት አስረድተዋል።

የሕዳሴ ግድቡን አጠናቆ ለትውልድ ለማውረስ እየተደረገ ባለው ርብርብ ላይ ወጣቱ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ተረድቶ የእድገት ጎዞው ወደ ኋላ እንዳይመለስ በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኘው ወጣት መስፍን ኃይለማሪያም እንደገለጸው፤ ወጣቱ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ እየሰራ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የተበረከተው የግድቡ ዋንጫ በየአካባቢው ሲዘዋወር ወጣቱ ቦንድ በመግዛት እያበረከተ ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ህዝቡን በመቀስቀስና በማስተባበር የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ወጣት ታየች ሞላ በበኩሏ ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጠንካራ ትግል ውስጥ ለአገሪቱ ሕዳሴ ስኬታማነት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቷን ገልጻለች።

ለግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አመራሮችና የወጣት አደረጃጀቶች መካፈላቸውን ኢዜአ ዘግቧል ፡፡