የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ከ8ሺ ሜጋ ዋት በላይ የሚያመነጩ ግድቦች ግንባታ ላይ መሆናቸዉን የዉሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ ::
ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ እየተፈጠረ ያለዉ የእዉቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሀገሪቱ በቀጣይ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ሙሉ በሙሉ ለመስራት የምትችልበት መደላድል እየፈጠረ ነዉ ብለዋል::
አገሪቱ አሁን ላይ በማመንጨት ላይ ያለውን 4ሺህ 284 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት እስከ ሁለተኛዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ድረስ ወደ 17 ሺ ሜጋ ዋት ለማድረሰ እየተሰራ እንደሆነም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል::
የሀይል ፍላጎት አቅርቦቱን ለማሟላት እንደ ነፋስና ጸሐይ ኃይል ያሉ አማራጭ የታዳሽ ሀይል ምጮችን የመጠቀሙ እንቅስቃሴም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል ::
ኢትዮጵያ ከውሀ ብቻ እስከ 45ሺ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት ዓቅም እንዳላት ይታወቃል-(ኢቢሲ) ፡፡