የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ለማከናወን ካቀደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራዎች 90 በመቶውን ማጠናቀቁን አስታወቀ ።
የክልሉ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ መና ለዋሚኮ እንደገለጹት በክልሉ እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራዎች እስካሁን ድረስ 405 ሺ ሄክታር መሬትን መሸፈን ተችሏል ።
እንደ አቶ መለሰ ገለጻ በክልሉ ለተፈጥሮ ጥበቃ የዘመቻ ሥራ ለማሳተፍ ከታቀደው 5 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 82 በመቶ የሚሆነውን ማንቀሳቀስ ተችሏል ።
በክልሉ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃሥራ አፈጻጻም ለማስመዝገብ ለተመረጡ አርሶ አደሮች በእርከን ሥራ ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ሥልጠና መሠጠቱንም አቶ መለሰ አያይዘው ገልጸዋል ።
በክልሉ እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራ በ136 ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ፣ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች ቀጥተኛ ታሳትፎ እያደረጉ መሆኑ ተመልክቷል ።
በዘመቻ ሥራው ከአካባቢዎቹ የአየር ፀባይ ጋር የሚሄዱ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ፣ ችግኞችን መንከባከብና ትናንሽ የመስኖ ሥራዎችን ዲዛይን የማድረግ እንቅስቃሴዎች መካተታቸውን አቶ መሰለ ጠቁመዋል ።
በክልሉ የዘንድሮ ዓመት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራዎች ውስጥ ከዓምና ካጋጠሙ ችግሮች በመማርና ከተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እያተደረገ እንደሚገኝ አቶ መሰለ አብራርተዋል ።