የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብት በአምራች ኢንዱስትሪ በስፋት እንዳይሰማራ ማነቆ ናቸው የተባሉ ችግሮችን የሚያሳይ ጥናት ይፋ ሆነ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሚመሩት መድረክ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ለከፍተኛ አመራሮች፣ ለተመራማሪዎችና ለባለድርሻ አካላት ይፋ ያደረገው ይህ ጥናት፥ የሀገር ውስጥ የግል ባለሀብቱ በዘርፉ ከመሰማራት አንፃር ያሉት እድሎች፣ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ ነው።
በጥናቱ የማበረታቻ ስርዓቶች፣ የገቢ ግብር ምጣኔ፣ የመንግስት የግዥ ስርዓት እና መሰል ችግሮች ለዘርፉ የእድገት ማነቆ መሆናቸው ተመላክቷል።
ማበረታቻዎቹ በራሳቸው በተንዛዙ አሰራሮች ምክንያት ለግል ባለሃብቱ ተደራሽ ያለመሆን፥ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች ለዘርፉ ማነቆዎች ናቸው ከተባሉት ችግሮች መካከል ተጠቅሰዋል።
ሀገሪቱ ለሁሉም ዘርፎች የገቢ ግብር የምታሰላው 30 በመቶ መሆኑም ከበርካታ ሀገራት አማካይ የገቢ ግብር ምጣኔ (17 በመቶ) ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑ ዘርፉ የግል ባለሃብቶችነ የሚያበረታታ አከመሆኑን ያሳያል ነው የተባለው።
ከግብር ተቀናሽ የሚሆኑ ወጪዎች በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውም ሌላኛው የዘርፉ እድገት ማነቆ መሆኑን ነው ጥናቱ ያመላከተው።
ከጉምሩክ ቀረጥ እና ነፃ አሰራሮች ጋር ተያይዞም ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተብራርቷል።
ከውጭ በጥሬ እቃነት ለሚገቡ እቃዎች እና ከውጭ ለሚገቡ ያለቀላቸላቸው ምርቶች የሚጠየቀው ታሪፍ ተመሳሳይ መሆንም አምራቾችን አያበረታታም የሚለው ተጠቅሷል።
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የተንዛዛ በሆነበት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የሎጂስቲክ እና መሰል ችግሮች በሚስተዋሉበት ሁኔታ ኢንዱስትሪዎች የግብር እፎይታ ጊዜያቸውን በአግባቡ ሳይጠቀሙባቸው ያልቃሉየተባለው ፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ እና ከመዲናዋ ውጭ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚሰጣቸው የግብር እፎይታ ጊዜ ተመሳሳይ መሆኑ ሌላው ማነቆ ሆኖ ተለይቷል።
የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦት ችግር፣ የኢንዱስትሪዎች አመራሮች የማስፈፀም አቅም ደካማ መሆን፣ የምርት ጥራት እና ደረጃ መውረድ፣ የህገወጥ ንግድ፣ ተመሳስለው የተሰሩ እቃዎች መበራከት እና መሰል ችግሮችም ለዘርፉ የእድገት እክሎች ናቸው ብሏል ጥናቱ።
ጥናቱ ከለያቸው የዘርፉ ማነቆዎች ባሻገር የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።
በዚህም ለማምረቻ ዘርፉ ዝቅተኛ የባንኮች የወለድ ምጣኔ ማስቀመጥ፣ ለዘርፉ የተለየ የገቢ ግብር ምጣኔ መተግበር፣ የግብአት፣ የቀረጥ እና ታክስ ስርአትን ማሻሻል እንዲሁም የግብር ተቀናሽ ወጪዎችን ማበረታታት በመፍትሄነት ተቀምጠዋል።
ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የባንክ ብድርን ተደራሽ ማድረግ ፣ ተገቢ ያልሆነ አለም አቀፍ የንግድ ውድድርን ለመግታት የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀትም ከተጠቀሱት የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከል ይገኝበታል።
የመንግስት የግዥ ስርአትም ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ እንዲሰጥ አስገዳጅ ስርአት መዘርጋት ይገባል የሚለው ተጠቅሷል።
የጥናቱ ግኝቶች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውይይት እያደረጉበት ሲሆን፥ በቀጣይ ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያዎችንም ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውይይቱ ከስአት በኋላ ሲቀጥል በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያሉ እድሎች፣ ተግዳሮቶችና የፖሊስ አማራጭ ሀሳቦች የሚያሳይ ጥናት ቀርቦ ምክክር ይደረግበታል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።