ሀሰተኛ ሰነድ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የስራ ተቋራጮች ላይ ውሳኔ ማስተላለፉን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳያሳድሱ እና በሀሰተኛ ሰነድና ማስረጃ ከደረጃ ወደ ደረጃ ሽግግር አድርገዋል በሚል በ2006 ዓ.ም 177 የስራ ተቋራጮችን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አግዶ እንደነበር የተጠቀሰው ፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና እና የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባደረጉት ክትትል ከ177 ተቋራጮች ውስጥ 141 ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ከደረጃ ወደ ደረጃ መሸጋገረቻውን እና ፈቃድም አለማደሳቸውን አረጋግጧል፡፡
የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሐመድ 141ዱ የስራ ተቋራጮች ከደረጃ 4 እሰከ 10 ያሉና ታዳጊ በመሆናቸው ህዝብና መንግስትን ይቅርታ ጠይቀውና ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የስራ ተቋራጮች በሰሩት ስራ ልክ በህግ ሊጠየቁ ይገባ ነበር የሚል ሃሳብ የተነሳ ሲሆን፤ የስራ ተቋራጮቹ ሲጀምሩ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው የተንቀሳቀሱ በሂደት ደግሞ በሀሰተኛ ሰነድ ከደረጃ ወደ ደረጃ የተሸጋገሩ እና ታዳጊ በመሆናቸው ሙሉ ለሙሉ ከመዝጋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታርመው እንዲሰሩ ማድረጉ ሐገርንም ተቋራጮቹንም ይጠቅማል በሚል ሃሳብ እንደሆነ ኢንጅነር አይሻ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉትም 36ቱ የስራ ተቋራጮች ምንም እንኳ በፌደራል ደረጃ የተመዘገቡ ቢሆንም ምንም ማስረጃ የሌላቸው አየር በአየር የሚሰሩ በመሆናቸው የማጣራት ስራው ይቀጥላል ብለዋል ፡፡
ከዚህ ውጭ ከደረጃ 1 እስከ 3 ያሉ የስራ ተቋራጮችን በተመለከተ የማጣራት ስራው እየተከናወነ በመሆኑ ሲጠናቀቅ ይፋ ይደረጋል ነው ያሉት ፡፡
የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና የስነ- ምግባርና ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ባደረጉት ጥናት በፌደራል ደረጃ ከ14 ሺህ በላይ የስራ ተቋራጮች በተለያየ ደረጃ የተመዘገቡ ቢሆንም በየዓመቱ ተከታትለው ፈቃድ የሚያሳድሱት ግን ከ6 መቶ በላይ እንዳልሆኑ ነው የተመለከተው ፡፡
የስራ ተቋራጮች ሀሰተኛ ሊብሬ፣ የባንክ ብድር መያዣ ደብዳቤዎች፣ የትራንስፖርት ባለስልጣን ደብዳቤዎችን በማቅረብ ፈቃድ ማውጣት መኖሩ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በቀጣይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና አሰራሮችን በማስተካከል ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመስራት ዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል-(ኢብኮ) ፡፡