ጀርመን በተለያዩ የልማትና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢትዮጵያን መደገፍ እንደምትፈልግ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ገርድ ሙለር ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትሩን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
ዶክተር ገርድ ሙለር እንዳሉት፤ ጀርመን ኢትዮጵያን በቴክኒክና ሙያ ትምህርት፣ በግብርናና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመደገፍ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማሳደግ ትፈልጋለች።
የአገሪቱን የግብርናና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ እንቅስቃሴ ለመደገፍ የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ እናደርጋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ጀርመን አጋር እንደምትሆንም ሚኒስትሩ ገርድ ሙለር ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ጀርመን የምታደርገው ድጋፍ ኢትዮጵያ በምትከተለው የግብርናና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ላይ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
"ጀርመን በግብርናው ዘርፍ ያላት ልምድና ተሞክሮ የልማት አቅጣጫችንን የሚደግፍ በመሆኑ ትብብሩን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በሚያደርጉት ድጋፍና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ውይይት አድርገው መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል።
የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያና ጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1905 የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ- (ኢዜአ) ።