የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከሎተሪ ሽያጭ 125 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ገቢውን ለመሰብሰብ ትናንት ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ሎተሪው ከሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት ገበያ ላይ የሚውል መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
የጽህፈት ቤቱ የፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ የአካባቢ ጥበቃና ስነ-ጥበብ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተካ እንዳሉት ሎተሪው በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቅርንጫፎች፣ በግድቡ ምክር ቤት ጽህፈት ቤቶች፣ በመንግስት ተቋማት፣ በሲቪክ ማህበራትና በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ይሰራጫል።
በመሆኑም የመንግስት ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት የታቀደውን ገቢ ለማሰባሰብ ሰራተኞቻቸውንና አባሎቻቸውን በማስተባበር እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ተቋማቱ ከሚሸጡት የባለ 25 ብር ቲኬት 15 በመቶ የሚታሰብላቸው ስለሆነ ገቢውን ከማሰባሰብ በተጨማሪ ራሳቸውን የሚያጠናክሩበት ዕድል የሚከፍትላቸው በመሆኑ ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ነው ያሉት አቶ ሰለሞን፡፡
ሎተሪው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን በአንደኛ ዕጣ ባለ ሶስት መኝታ መኖሪያ ቤት፣ በሁለተኛ ዕጣ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፒክ አፕ መኪና፣ በሶስተኛ ዕጣ ባለሁለት መኝታ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎችንም ሽልማቶች ይዟል-(ኢዜአ) ፡፡