የሀረሚያ ዩኒቨርስቲ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ፎረምን የምስራቅ ንዑስ ፕሮግራም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር ማቋቋሙን አስታወቀ ።
በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ለዋሚኮ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው በአፍሪካ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ላይ የሚያተኩር ፎረምን ያቋቋመው ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከአፍሪካ የግብርና ቴክኖሎጂ ፋውንዴሽን ጋር በመተባባር ነው ።
ፎረሙ መቋቋሙ በባዮቴክኖሎጂ ዙሪያ መደበኛና ተዓማኒ የሆነ የመረጃና እውቀት ልውውጥን ለመፍጠር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ንጉሴ በማቋቋሙ ሥራ ዩኒቨርሰቲው አመራር ፣ መምህራንና ተማሪዎች ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል ።
የፎረሙ ንዑስ ፕሮግራም በዩኒቨርስቲው እንዲቋቋም መደረጉ ተመራማሪዎች ፣ መምህራንና ተማሪዎች በባዮቴክኖሎጂ ዙሪያ የተለያዩ አገራትን ምርጥ ተሞክሮዎችንና ልምዶችን በጋራ በመካፈል በዘርፉ አቅምን ለመገንባት እንደሚያስችል ፕሮፌሰሩ አያይዘው ገልጸዋል ።
የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ ለግብርና ምርት ዕድገት ተግዳሮት የሆኑትን የአየር ንብረት ለውጥና የሰብል በሽታዎችን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚጫወተው ሚና የላቀ በመሆኑ ትኩረት ይገባዋል ።