የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሶስት የልማት ፕሮጀክቶች ትግበራ የሚውል 645 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጠ።
ፕሮጀክቶቹ የውሃና ሳኒቴሽን፣ የንግድና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት እንዲሁም የምርቶች ጥራት ማሻሻያ ናቸው።
የብድር ስምምነቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንዲሁም በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ካሮልይ ተርክ ተፈራርመዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በ23 ከተሞች ተግባራዊ ለሚሆነው የውሃና ሳኒቴሽን ትግበራ 445 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን አሁን በአገሪቱ ሁሉም ከተሞች ያለውን የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ወደተሻለ ደረጃ ያሳድገዋል ተብሏል።
የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን በማዘመን ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሞጆ ደረቅ ወደብን ለማሻሻል 150 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል።
ይህም የሞጆ የወደብ አገልግሎትን በማሻሻል ገቢና ወጪ ምርቶችን ለማቀላጠፍ ያግዛል።
የምርት ጥራቶችን ለማስጠበቅና ለማሻሻል 50 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን ጥራትን የሚከታተሉና የሚቆጣጠሩ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል(ኢዜአ )።