የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ለተጠቃሚዎች አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ማቅረቡን የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የገበያ መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢትሳ ደሜ ለዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት የትንሳኤን በዓል ተከትሎ ሊፈጠር የሚችልን ሸመታ ዋጋ መጨመር ለመከላከል እንዲቻል አዲስ አበባ በሚገኙ ከ500 በላይ በሚሆኑ በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት የተለያዩ ሸቀጦች ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሽንኩርት በ12 ብር፣ ዱቄት ከ9-12ብር፣ እንቁላል 3ብር፣ ዶሮ እስከ 200 ብር፣ ስኳር በኪሎ 18 ብር ከ40 ሳንቲም እንዲሁም ባለ ሶስት ሊትር ዘይት በ77ብር ከ40 ሳንቲም እንደሚሸጥ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ጋር በተፈጠረው ገበያ ትስስር የድልብ ሰንጋዎች ሥጋን በኪሎ ከ80 ብር እስከ 120 ብር ለመሸጥ ዝግጅቶች እንደተጠናቀቁም ታውቋል፡፡
በስርጭት በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላትና ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ መምርቶቹ ለሕብረተሰቡ በቀጥታ ሚደርሱበት ሁኔታም ክትትል እንደሚደረግበት ታውቋል፡፡
አቶ ኢትሳ አክለው እንደገለፁት ምርቶቹ በበቂ መጠን ስለተዘጋጁ ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ ግብይቱን እዲያከናውን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡