በቤንች ማጂ ዞን ተምች በ4 ሺህ 760 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ ጉዳት አደረሰ

 

በቤንች ማጂ ዞን የተከሰተ ተምች 4 ሺህ 760 ሄክታር ላይ በነበረ የበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡የመምሪያው ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ደስታ ግርማዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ተምቹ  ለመጀመሪያ ጊዜ በዞኑ የታየው መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ሸዋ ቤንች ወረዳ ኩካ ቀበሌ ውስጥ ነው።

በአሁኑ ወቅት የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በዞኑ አስር ወረዳዎች በመሚገኙ በ221 ቀበሌዎች ላይ መዛመቱን አመልክተዋል።

ተምቹ ከ12 ሺህ የሚበልጡ አርሶአደሮች ማሳ ላይ በ4 ሺህ 760 ሄክታር መሬት የነበረ የበቆሎ ሰብልን ማጥፋቱን ጠቅሰዋል ።

የተምቹን ስርጭት ለመከላከል በ2 ሺህ 868  ሄክታር መሬት ላይ 5 ሺህ 764 ሊትር ጸረ -ተባይ መድኃኒት መረጨቱንም ተናግረዋል ።

"ተምቹን ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ተምቹ በአንድ ጊዜ  እስከ 2ሺህ 500 እንቁላል በመጣል በፍጥነት የሚራባ መሆኑ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል " ብለዋል ።

አርሶአደሩ በማሳው ላይ ክትትል በማድረግ ተምቹን በባህላዊ መንገድ በመግደል ጉዳቱን ለመቀነስ የራሱን ጥረት እንዲያደርግ መደረጉንም ወይዘሮ ደስታ ጠቅሰዋል ።

በደቡብ ቤንች ወረዳ የፋኒቃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ካህሱ አብርሃ በሩብ ሄክታር ማሳቸው ላይ ቀድመው የዘሩት የበቆሎ ሰብል ተምቹ  ባደረሰበት ጉዳት መጥፋቱን ጠቁመዋል ።

የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ጸጋዬ ተክለእግዚአብሄር  በበኩላቸው፣ ተምቹ በአካባቢያቸው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ የብዙ አርሶአደሮች ማሳ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

"ተምቹ ቀደም ሲል የዘራሁትን በቆሎ አውድሞብኛል፣ አዲስ በዘራሁት ማሳ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ክትትል እያደረኩ ነው’’ ብለዋል፡፡

"ከዚህ ቀደም በአካባቢያችን እንደዚህ ሰብልን በፍጥነት የሚያጠፋ ተባይ ተከስቶ አያውቅም፤ ይህ የመጀመሪያ ነው" ያሉት ደግሞ በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የሸሸቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ባስክን ወሽከራ ናቸው፡፡

በዞኑ የተከሰተው ተምች ፉል አርሚ የተሰኘ መጠሪያ ያለውና ያልተለመደ ዝርያ   መሆኑ  ነው-(ኢዜአ) ፡፡