ድርጅቱ ለሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ተቋም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ለሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ተቋም የነጻ ትምህርት ዕድልን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያደርግ አስታወቀ።

ዋና ጸኃፊው ዶክተር ታሌብ ሪፋይ ተቋሙን ሲጎበኙ እንደተናገሩት ድርጅቱ በየዓመቱ ለአምስት ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጣል።

በተጨማሪም የአሰልጣኞችና የአስተዳደር አካላትን አቅም ለማጎልበት ከዓለም 11 የቱሪዝም ስልጠና ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጠር እናደርጋለን ያሉት።

ዋና ጸሐፊው ከተቋሙ ጋር የጉብኝት፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እናደርጋለንም ብለዋል።( ኢዜአ)

በተለይ በዓለም ቱሪዝም ድርጅት በሚሰሩ ጥናቶች ላይ ተቋሙ ተሳታፊ እንዲሆን እናደርጋለንም ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም ከዚህ የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት ከኛ ጋር በቅርበት መስራት ተቋሙን አሁን ካለበት ወደተሻለ ደረጃ ለማምጣት ይረዳል ነው ያሉት።

ዶክተር ታሌብ "አሁን ወደ ኢትዮጵያ 13 ሆነን ነው የመጣነው እኔ ግን 13 ሚሊዮን ሆነን ብንመጣ ደስ ይለኝ ነበር፤ ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ከመባልም ያለፈች አገር ናትና" ብለዋል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ በበኩላቸው ለአገሪቱ የቱሪዝም ዕድገት ተቋሙ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉንና በዘርፉ ያሉ አብዛኞቹ ባለሙያዎች የተቋሙ ሰልጣኞች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ተቋሙ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የልዕቀት ማዕከል በመሆን ስልጠናና ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም 200 አሰልጣኞች ማሰልጠኑንና ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ በተሰጠ ድጋፍ 4 ሺህ 129 ሰልጣኞች ተቀብሎ በተለያዩ ዘርፎች እየሰለጠነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ እስካሁን 11 ሺህ ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን ያሉትን የስልጠና ዘርፎች ከሁለት ወደ 13 ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

የሚሰጠው ስልጠና ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር በቂ አይደለም ያሉት አቶ አሸብር የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።(ኢዜአ)