በአገሪቱ በአራት ክልሎች የሚቋቋሙት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ400ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለዋሚኮ እንደገለጹት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው የግንባታ ሥራቸውን ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተካሄደባቸው ያሉት አራት ሞዴል የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው ።
ሞዴል አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በአማራ ክልል በቡሬ አካባቢ ፣ በትግራይ በሁመራ ፣ በኦሮሚያ አዳሜ ቱሉና በደቡብ ክልል በይርጋለም አካባቢ የሚገነቡ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አሰፋ ለግንባታ ሥራው የሚውለውን 1ሺ ሄክታር መሬት እያንዳንዱ ክልል አቅርቧል ብለዋል ።
በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ውስጥ የሚገቡት 80በመቶ የሚሆኑት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እንደሚሆኑ የጠቀሱት አቶ አሰፋ 20 በመቶ የውጭ አገር ባለሃብቶች በፓርኮቹ ገብተው እንዲሠሩ ይፈቀዳል ብለዋል ።
መንግሥት አራቱን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስገንባት ከዘላቂ ልማት ግብ ፈንድ የ250 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ አግኝቷል ያሉት አቶ አሰፋ ሁሉም ክልሎች ለፓርኮቹ ግንባታ የሚውል ገንዘብም እንደሚመድቡ አክለው ገልጸዋል ።
የሚገነቡት አግሮ ኢንዱስትሪዎች በውስጣቸው የምግብ ማቀነባባቂያ ኢንዱስሪዎች ፣ በገጠር ግብዓት ማቅረቢያና ግብዓት መሰብሰቢያ ማዕከላት ያካተቱ እንደሚሆኑ አቶ አሰፋ አመልክተዋል ።
አግሮ ኢንዱስሪዎቹ በአካበቢያቸው የሚገኙት የግብርና ውጤቶችን በጥሬ እቃነት በመጠቀም የሚያመርቱ ሲሆን በፓርኮቹ አካባቢ እስከ 100 ኪሎሜትር የሚደርሱ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገምቷል ።
መንግሥት የአምራች ዘርፉን ለማሳደግ በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የመሠረተ ልማት የተሟላላቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስገንባት ላይ እንደሚገኝ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል ።