በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአይሲቲ ኤክስፖ ሊካሄድ ነው

የመጀሪያውን የአይሲቲ (ኢንፎርሜሽንና ኮሚኑኬሽን ቴክኖሎጂ) ኤክስፖ በሚሌኒየም አዳራሽ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

ሚንስቴር ዴኤታ ጌታቸው ነጋሽ ዛሬ በካፒታል ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ከሰኔ 21-25፣2009ዓ.ም.የሚካሄደው ኤክስፖው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የዕውቀትና ክህሎት ሽግግርን ለማጠናከርና በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን ለማበረታታት እንደሚስችል ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ኤክስፖው በአይሲቲ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ተማሪዎችን፣ ባለሙያዎችንና የአነስተኛና ጥቃቅን አንቀሳቃሾችን ለማበረታታት የሚያስችሉ ዓላማዎችን ያነገበ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

“ዲጂታል ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ኤክስፖው ኢትዮጵያ ከግብር ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ አይሲቲ ያለው ሚና ጉልህ ከመሆኑ አንጻር ይህ ኤክስፖ ድርሻው ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡

ዲጂታል ግብርና፣ ዲጂታል ጤና፣ ዲጂታል ትምህርትና ዲጂታል ፋይናንስ በሚሉ ንኡስ መሪ ቃሎች በኤክስፖው የሚሳተፉ  ተመራማሪዎች፣ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችና ተማሪዎች የፓናል ውይይቶችና ክርክሮች እንደሚያካሂዱም ነው ያስታወቁት ፡፡

በኤክስፖው ላይ ሶፍትዌር ኩባንያዎች፣ ሃርድዌር ኩባንያዎች፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎች ከ200ሺህ በላይ ጎብኝዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ሲል ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡