ኮሚሽኑ የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር 7ነጥብ 6 ሚሊዮን መድረሱን አስታወቀ

በዘንድሮ የበጀት ዓመት ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች ቁጥር 7ነጥብ6 ሚሊዮን መድረሱን  የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዱ ለዋሚኮ እንደገለጹት በዘንድሮ ዓመት በዝናብ  እጥረት  ምክንያት ባስከተለው ድርቅ  ከጥር  ወር ጀምሮ 5ነጥብ6  ሚሊዮን  ወገኖች   ድጋፍ  ሲደርግላቸው  የቆየ ሲሆን ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የተረጂዎች ቁጥር በ2ሚሊዮን 68ሺ ማደጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል ።

እንደ አቶ ደበበ ማብራሪያ የድርቅ ተረጂዎች ቁጥር ያደገው በኦሮሚያ ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች በበልግ የተጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡና  ባለፈው የመኸር ወቅት በሦስቱም ክልሎች  የውርጭ ክስተት በሰብል ላይ  ጉዳት  በማድረሱ ምክንያት ነው ።

ኮሚሽኑ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ድረስ ለ2 ሚሊዮን 68ሺ ለሚደርሱ የድርቅ ተጎጂዎች የዕለት እርዳታ የሚውል ተጨማሪ 432ሺ 515 ሜትሪክ ቶን እህል ፣ አልሚ ምግብ፣ ጥራጥሬናዘይት ድጋፍ የሚያደርገው ከመጠባበቂያ የምግብ ክምችት በመውሰድ እየተሠራጨ መሆኑን  አቶ  ደበበ አመልክተዋል ።  

በዘንድሮ ዓመት በድርቅ ተጋላጭ  የሆኑት  አካባቢዎች  የቆላማናአርብቶ አደሩ የሚበዛባቸው አካባቢዎች  መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ  ደበበ   ለሰውና እንስሳት  የሚውል የውሃ እጥረትና የእንስሳት መኖን  ለማዳረስ  የተቀናጀ  እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን  ገልጸዋል ።

ድርቁ  በተባባሰባቸው በኦሮሚያ ክልል በቦረና፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ጉጂናባሌ   ዞኖች  በሁለት ዙር 260ሺ  እሥር የእንስሳትመኖ ሣር   መከፋፈሉን  እንዲሁም   በደቡብ ክልል ለጋሞጎፋ የሰገን ህዝቦች ዞን በአጠቃላይ 40ሺ እሥር የእንስሳት መኖ ሣር  መዳረሱን  አቶ  ደበበ አብራርተዋል  ።

በሶማሌና በአፋር  ክልሎች  መስኖ መሰረት ያደረገ የእንስሳት መኖ ልማት  እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደበበ  በአፋር በ1ሺ ሄክታር መሬት  ላይና በሶማሌ ክልል በ300  ሄክታር መሬት ላየ  የእንስሳት መኖ  በማልማት  ችግሩን ለመፍታት ጥረት  እየተደረገ ነው ብለዋል ።

በአገሪቱ  የተለያዩ  ክልሎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተውን  ድርቅ ለመከላከል በክልሎች  የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛውና  ልማታዊ ባለሃብቱ የበኩሉን የእርዳታ ድጋፍ  አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን  ኮሚሽኑ አመልክቷል ።