የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ( ዩኤስ ኤድ) 18 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የወተትና የወተት ግብዓት ማምረቻ ቁሳቁሶችን ለአራት ክልሎች በድጋፍ መልክ አበረከተ ።
ዩኤስ ኤድ ድጋፉን ያደረገው በአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የተሻለ ጥራት ያላቸው የወተትና የወተት ግብዓት ምርቶችን ለገበያ እንዲያቀርቡ የሚያስችል ነው ብለዋል ።
በድጋፍ የተሠጡት ቁሳቁሶች የወተት ማሸጊያ ፣ የወተት ማለቢያ ፣ ማቀዝቀዣ፣ ማከማቻ ፣ የወተት ማቆያ፣ መፈተሻና ማሞቂያ ማሽኖች መሆናቸው ተገልጿል ።
የዩኤስ ኤድ የልማት ተልዕኮ ዳይሬክተር ሌሊሴ ሪድ ድጋፍ የተደረጉትን ቁሳቁሶች የተለያዩ የፌደራል መንግሥት ተወካዮች ፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎችና አጋር ድርጅቶች በተገኙበት ለእንስሳትና አሳ ሃብት ሚንስትር ለሆኑት ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ አስረክበዋል ።
የቁሳቁስ ድጋፉን አስመልክተው የዩኤስኤድ ዳይሬክተር የሆኑት ሌሊሴ ሪድ እንደተናገሩት “ የእንስሳት ዘርፉን የተሻለና ትርፋማ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጋራ ተባባረው መሥራት ከቻሉ በዘርፉ ላይ የተሠማሩትን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ዘርፉ ለአገር ምጣኔ ሃብትም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ”ብለዋል ።
በቀጣይም ዘርፉን ለመደገፍ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በእንስሳትና የወተት ልማት ከተሠማሩ አካላት ጋር ተባባረው እንደሚሠሩና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል ።
ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ዘረፉን ለማሳደግ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተቀመጠው ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል ።