ምክር ቤቱ የታክስ ማጭበርበርና ተደራራቢ ግብርን የሚያስቀሩ ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከልና ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት ከተለያዩ አገራት ጋር ስምምነት የተደረሰባቸውን ረቂቅ አዋጆች መርምሮ አጸደቀ።

በዛሬው ዕለት የአገሪቱ ህግ ሆነው የጸደቁት ረቂቅ አዋጆች ከፖላንድ ፣ ከስሎቫኪያ ፣ ፍልስጤም ፣ ደቡብ ኮሪያ ፣ ሲንጋፖር ፣ ሞሮኮ ፣ ቆጽሮስና ሞዛምቢክ ጋር ስምምነት ተደርሶባቸው የተፈረሙ ናቸው። 

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ አበበ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት አስተያያት ከሰጡበት በኋላ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።

በስምምነቶቹ መሰረት በአንድ አገር ነዋሪ የሆነ ሰው ወይም ኩባንያ በሚኖርበትም ሆነ በሚሰራበት አገር ከሚያገኘው ገቢ የሚጠበቅበትን ታክስ  ለዚያው አገር መንግስት እንዲከፍል የሚያደርግ ነው።

የጸደቁት ረቂቅ አዋጆች በአገሮቹ መካከል የሚደረገውን የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነትም ያጠናክራሉ ተብሏል፡፡

የየአገራቱ ነዋሪዎች አንዱ በሌላው አገር የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት የሚያሳካና ተደራራቢ ግብርን በማስቀረት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነም ተገልጿል።

የበለጸጉ አገራት በመልማት ላይ ወዳሉት አካባቢዎች የሚያደርጉትን የኢንቨስትመንት፣ የካፒታል ፍሰት፣ የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና ክህሎት ሽግግር እንዲፈጠርም የሚያግዙ ናቸው ተብሏል።

የማምረት አቅም ከፍ እንዲል፣ ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠርና በውጭ ገበያ የሚኖረው ተሳትፎ እንዲጨምር ለማድረግም ያስችላሉ ተብሏል።

ምክር ቤቱ ባለፈው ወር መጨረሻ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የስምንቱን አገራት ረቂቅ አዋጆች ለዝርዝር እይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል-(ኢዜአ) ።