ኢትጵያና ቻይና የሁለትዮሽ  የስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸው ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ

ኢትጵያና ቻይና የሁለትዮሽ  የስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸው ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ይህን ፍላጎታቸውን ያረጋገጡት ከ30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከቻይናው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቼን ዚዶንግ ጋር ባካሄዱት ውይይት ነው፡፡

ሚኒስትሮቹ በምክክራቸው እንዳስታወቁት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማጠናከር የጋራ አቋም የያዙ ሲሆን፥ በተለይም በልማት ስራዎች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡ 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ  በውይይታቸው ቻይና  የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍና ድህነትን በመዋጋት እውነተኛ አጋርነቷን እያሳየች ትገኛለች ብለዋል፡፡

በዚህም ከቻይና ጋር በትብብር በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የቻይናው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቼን ዚዶንግ በበኩላቸው ሀገራቸው ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኑነት ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ አስውቀዋል፡፡

ዘገባው የሽንዋ ነው፡፡