የአገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል አለማደጉ የአገር ውስጥ ምርቶችን ተወዳዳሪነት እየጎዳ ነው

የአገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል አለመጎልበቱ  በአገር ወስጥ ምርቶች ተወዳዳሪነት ላይ ችግር ከመፍጠሩም በላይ  በአገሪቱ  ኢኮኖሚ ላይ  ጉዳት  እያስከተለ  መሆኑ ተገለጸ ።

ቢናሚስ የተባለ የግል ድርጅት ከመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ጋር በመተባባር  በዛሬው ዕለት በድሪም ላይነር ሆቴል  ባዘጋጀው ወርክ ሾፕ ላይ ህብረተሰቡ ምን ያህል  የአገር ውስጥ ምርቶች  እየተጠቀመ ይገኛል በሚል ርዕስ  ውይይት ተካሂዷል ።

በወርክሾፑ  የአገር ውስጥ ምርቶች ጥራት እየተሻሻለ ቢመጣም የተጠቃሚው አመለካከትና ግንዛቤ ባለመቀየሩ ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው  የአገር ውስጥ  ምርቶች ተጠቃሚነት በአነስተኛ ደረጃ እንደሚገኝም ተጠቁሟል ።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች  ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በወርክሾፑ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት መንግሥት የአገር ውስጥ  ምርቶች ተወዳዳሪነትን ላይ  የሚስተዋለውን  ችግር  ለመቅረፍ  ለመገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት እየሠራ  ይገኛል ።

የአገር ውስጥ  ምርቶችን  በህብረተሰቡ  ተፈልገው እንዲገዙ ለማድረግ   በጠቅላይ  ሚኒስትር  ኃይለማርያም  የሚመራ  እንቅስቃሴ  መጀመሩን  የጠቆሙት  ዶክተር ነገሪ  የአገር ውስጥ ምርቶች ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ የሚከናወኑት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል ።

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች  ከጊዜ  ወደ ጊዜ  ጥራታቸው እየተሻሻሉ  ቢመጡም   ህብረተሰቡ   ለውጭ አገራት  ምርቶች  በሚሠጠው  የተሳሳተ ቦታ ምክንያት   በተጋነነ  ዋጋ የጥራት ደረጃቸው  ዝቅተኛ የሆኑ ምርቶችን ሲገዛ እንደሚስተዋል በወርክ ሾፑ ገልጸዋል  ።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው  ምርቶች  በመጠን አነስተኛ  መሆናቸውንና  ወደ አግር ውስጥ  የምታስገባቸው  ምርቶች  ግን ከፍተኛ  መጠን ያላቸው በመሆኑ ምክንያት  ለረጅም ጊዜ  ለንግድ ሚዛን መዛባት ችግር ተጋላጭ  መሆኑም  በወርክሾፑ ተጠቅሷል ።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ  የገቢ ንግድ 16 ቢሊዮን  ዶላር  መድረሱንና  አማካኝ ዓመታዊ  የወጪ  ንግድ  ከ 4  ቢሊዮን  አይበልጥም ።