ተማሪዎች ክረምቱን በልማትና አገራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ ስራዎች እንዲያሳልፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ምሩቃን ክረምቱን በልማትና አገራዊ አንድነት በሚያጎለብቱ ስራዎች እንዲያሳልፉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ተማሪዎች በክረምት ወቅት በርካታ ለአገር ጠቃሚ ስራዎችን መከወን ይችላሉ።

ከዚህ ውስጥም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግኝ በመትከልና በጽዳት ስራ ላይ በመሳተፍ አካባቢን መጠበቅ ትልቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ተማሪዎች ይህን በማድረግ ከእነርሱ በታች ያሉ ተማሪዎችን በማስተማርና በማሰልጠንም ክረምቱን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎች በክረምት የእረፍት ጊዜያቸው በዘመቻ መልክ ተደራጀተው በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ አገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች መስራት ይችላሉ ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የመፈራረጅ አዝማሚያ መኖሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማሪዎች የባህልና ኑሮ ዘይቤ ልውውጥ በማድረግ በመቀራርብ አገራዊ አንድነትን እንዲፈጥሩ አሳስበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በመሄድም ማስተማርና የመንግስትን ስራ ቢያግዙ  ሲሉም ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ መሰማራት የሚፈልጉትን የማደራጀትና የማሰማራት ስራ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ይሰራሉ ብለዋል። (ኢዜአ)