በኢንዱስሪው ዘርፍ የሚስተዋለውን የሠው ኃይል ክፍተት ለመሙላት አስተዳደሩ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንደሚገነባ አስታወቀ

በኢንዱስሪው ዘርፍ የሚስተዋለውን የሰለጠነ የሠው ሀይል ክፍተት ለመሙላት በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ክፍለ ከተሞች አዳዲስ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እንደሚገነቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ አስታወቁ፡፡

ከንቲባ ድርባ ኩማ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ቢሮ ያስገነባቸውን የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ወርክሾፖች፤ የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን እና የኢንፎርሜሽን ኮሚዮኒኬሽን ማዕከላትን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ተመርቀው የተከፈቱት ማዕከላትም የብረታ ብረት፤ የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች ፤ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ወርክሾፖችን ያቀፉ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ማዕከላቱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ሀይልና በግብአት አቅርቦት ለማሳደግ በየደረጃው ያሉ ክፍተቶችን የመሙላት ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡

በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታየውን የሰለጠነ የሠው ሃይል ለማፍራት በከተማዋ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች አዳዲስ የፖሊቴክኒክ ኮሌጆች እንደሚገነቡ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ቢሮ ሀላፊ አቶ ዘሩ ስሙር በበኩላቸው አዳዲስ የተገነቡት ወርክሾፖች የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈልገውን ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ የፊዴራልና የከተማዋ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡ (ምንጭ፤ አዲስ አበባ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)