አየር መንገዱ ኤሲኤም ከተሰኘ የጀርመኑ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር ለመሥራት ስምምነት ፈረመ

አየር መንገዱ በአውሮፓ ሰፊ እውቅና ካለውና ኤ ሲ ኤም ከተሰኘ የጀርመኑ የአውሮፕላን የውስጥ አካላት አምራች ኩባንያ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት በአዲስ አበባ ፈርሟል።

የወንበር አልባሳትን፣ የደህንነት ቀበቶን፣ ምንጣፍንና ሌሎች የአውሮፕላን የውስጥ አካላት ማምረቻው ኢትዮጵያ ውስጥ ተገንብቶ ከአራት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።                                                

በተደረሰው ስምምነት መሠረት አየር መንገዱ የአውሮፕላን የውስጥ አካላቱን ምርት የሚያቀርበው ለኤ ሲ ኤም ኩባንያ መሆኑም ተገጿል።   

ማምረቻው ሥራ ሲጀምር ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ከመጡት የጨርቃጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ለዘርፎቹ እድገት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አስታውቀዋል።   

የስምምነቱ ዓላማ በአውሮፕላን ሞተርና በሌሎች የውስጥ አካላት ጥገና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የኢትዮዽያ አየር መንገድ የጥገና አቅም ማሳደግ መሆኑንም ተናግረዋል።                          

አየር መንገዱ የአውሮፕላን የውስጥ አካላትን ለማምረት የሚያስችሉ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ አገሮች በማስገባት ሥራውን የሚጀምር ሲሆን በሂደት ግን ጥሬ እቃዎችን ጭምር የማምረት እቅድ እንዳለው አቶ ተወልደ ገልፀዋል።

በአየር መንገዱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገነባው ማምረቻ ወደፊት ወደኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሸጋገርበት ሁኔታ እንዲፈጠር አየር መንገዱ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የጀርመኑ ኤ ሲ ኤም ኤሮስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አራሽ ኖሻሪ በበኩላቸው ቅድመ ሥራዎች ተጠናቀው በሶስትና በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የአውሮፕላን የውስጥ አካላት መመረት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የአፍሪካ አህጉርን በአየር ትራንስፖርት አንድ የማድረግ ዓላማ ይዞ ከሚሠራውና በየጊዜው እያደገ ከመጣው የኢትዮዽያ አየር መንገድ ጋር መሥራት ለኩባንያውና ለጀርመን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።