የባንኮች ተቀማጭ ሒሳብ ከ688 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ብሔራዊ ባንኩ አስታወቀ

በኢትዮጵያ የባንኮች አጠቃለይ ተቀማጭ ሒሳብ ከ688 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገልጸዋል።

በባንኩ የገንዘብና ፋይናንስ ትንተና ዳሬክተር አቶ ሙሉነህ አያሌው እንደገለጹት የባንኮችን ተቀማጭ ሒሳብ ለማሳደግ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።

የባንኮችን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ከተወሰዱ እርምጃዎች ውስጥም አንዱ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

ቆጣቢዎች የሚያገኙትን የወለድ ጥቅም ለመጨመር የወለድ መጠን ከ5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ከፍ ማድረጉ ሌላኛው ምክንያት ነው ይላሉ።

በዚህም እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም ድረስ በአገሪቷ የባንኮች አጠቃለይ ተቀማጭ ሒሳብ ከ688 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ነው የተናገሩት።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከ529 ቢሊዮን ብር በላይ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት 30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት።

ባንኮች ከቁጠባ የሚሰበስቡትን ገንዘብ ለተለያዩ ወጪዎች በብድር መልክ እንደሚሰጡም ይታወቃል።

በመሆኑም የሚሰበስቡት ተቀማጭ ሒሳብ ሲያድግ የማበደር አቅማቸው ከፍ እንደሚል የዘርፉ ምሁራን ያስቀምጣሉ።

እስከ ተጠቀሰው ጊዜም በባንኮች የተሰጠው የብድር ክምችት መጠን ከ646 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ነው አቶ ሙሉነህ የገለጹት።

ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ22 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ 18 ባንኮች፣ 13 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ከ18 ሺህ በላይ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። (ኢዜአ)