የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የአሠራር ሥርዓት ጥናት መጠናቀቁንና በቅርቡ ለህዝብ ይፋ ተደርጎ ወደ ሥራ እንደሚገባ የብሔራዊ ባንክ አስታወቀ ።
የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት አገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎም በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ገንዘቦች ወደ ባንክ እየመጣ ስለመሆኑም የተናገሩት ዶክተር ይናገር በቅርቡ ዝርዝር መረጃው ለህብረተሰቡ ይፋ ይደረጋል ብለዋል ።
በአገር ውስጥ ባለሃብቶችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዙ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግሥት ተባብረው እንዲሠሩም ዶክተር ይናገር ጥሪ አስተላልፈዋል ።
ዶክተር ይናገር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይትም ከባለሃብቶች ለቀረቡላቸው ቅሬታዎች በሠጡት ምላሽ እንደገለጹት በቅርቡ በአገሪቱ ለውጭ ምንዛሪ እጥረት መከሰት የውጭ ምንዛሪ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት ይጠቀሳል ብለዋል ።
በተጨማሪም ወቅቱ የሚጠይቀውን መስፈርት ያላሟሉ መመሪያዎችና አሠራሮች እንዲሁም ኃላፊነት የጎደላቸውና ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ የሠጡ የብሄራዊ ባንክ አመራሮችና ሰራተኞች ለተፈጠረው ችግር የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበረከታቸውን ገልጸዋል ፡፡