በአንበሳ ባንክ ያለበቂ ጥንቃቄ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ገንዘብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

በአንበሳ ባንክ ያለበቂ ጥንቃቄ በአፋር ክልል ሲንቀሳቀስ የተገኘ 17 ሚሊዮን በላይ ብር መያዙን ፖለስ አስታወቀ፡፡

ችግሩ የተፈጠረው ከጥንቃቄ ጉድለት በመሆኑ በቀጣይ ስህተቱን እንደሚያርም ባንኩ ገልጿል፡፡

የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል የስራ ሂደት አስተባባሪ ኮማንደር መሐመድ ኡትባን ለኢዜአ እንደገለጹት ገንዘቡ የተያዘው ሐምሌ 27/2010 . ከአይሳኢታ እና  ዶችኦቶ  አንበሳ ባንክ ቅርንጫፎች ወጪ ተደርጎ ያለፖሊስ አጃቢ  ወደ ሰመራ ቅርንጫፍ ለማንቀሳቀስ በሚል ሲሞከር ነው፡፡

ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በባንኩ ሰራተኞች አማካኝነት ሲንቀሳቀስ የተገኘው ገንዘብ  በህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ባደረገው ክትትል ዲችኦቶ ከተማ እንደደረስ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

ከተያዘው 17 ሚሊዮን 360 ብር ውስጥ 12ሚሊዮን ብር  ከዶችኦቶ ቅርንጫፍ ቀሪው  ከአይሳኢታ የወጣ ነው፡፡

ባንኮች ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ ቅድሚያ ለብሄራዊ ባንክና ተያያዥ የመንግስት ፋይናንስ ተቋማት ተቆጣጣሪ አካላት አሳውቀው በፖሊስ መታጀብ እንዳለበት  ህግ እንደሚያስገድድ ኮማንደሩ አመልክተዋል፡፡

ሲንቀሳቀስ የተገኘው ገንዘብም ከዚህ አግባብ ውጭ በመሆኑ ህገወጥ ያደርገዋልብለዋል፡፡

ኮማንደሩ እንዳሉት በታርጋ ቁጥር ኮድ3- 40315 . ባለሁለት ጋቢና ሃይሎክስ ተሽከርካሪ ገንዘቡን ጭነው ሲያንቀሳቅሱ የተገኙ አራት የባንኩ  ሰራተኞችም ተይዘው ለተጨማሪ ምርመራ ለፌዴራል ፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡

የሀገሪቱን የለውጥ እንቅስቀሴ ተከትሎ በተለያዩ አካላት የሚካሄድ ህገወጥ የሰዎችና የገንዘብ እንዲሁም የጦር መሳሪያ  ዝውውር ለመቆጣጠር የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከአጎራባች ክልሎችና ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የአምበሳ ባንክ ኮርፖሬት ሰርቪስ ምክትል ፕሪዝዳንት አቶ ገብሩ መሸሻ እንዳሉት  ችግሩ የተፈጠረው ከዚህ በፊት በአካባቢው ካለው አሰተማማኝ ሰላምና ጸጥታ አንጻር ያለፖሊስ አጃቢ በውስጥ ሰራተኞች ብቻ ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ ገንዘብ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡

አሁን በሀገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ  ጋር ተያያዞ በውስጥ ሰራተኞቹ ማጀቡ ስህተት መሆኑን አምነው በቀጣይም ባንኩ እርምት በመውሰድ  ከፌዴራል ፖሊስ ጋር  በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

15 ቀን በፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ 24ሚሊዮን ብር በላይ  ወደ ደሴ ቅርንጫፍ ሲንቀሳቀስ በባቲ ከተማ ፖሊስ ተይዞ በጸጥታ አካል መታጀብ እንዳለበት በመተማመን ችግሩን መፈታቱን አስታውሰዋል፡፡