አርሶ አደሩን ወደ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ለማሸጋገር ምሁራን በዕውቀታቸው መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

አርሶ አደሩን ወደ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ምሁራን በዕውቀታቸው መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡

በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ የዘርፉ ምሁራንን ያሳተፈ የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ ትላንት በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚህ ወቅት እንዳሉት በግብርናው ዘርፍ ክልሉ  እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ነው።

“በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳትና ተፈጥሮ ሃብት ያለው እምቅ ሃብት ከክልሉ አልፎ ለሀገር የሚተርፍ ነው”ብለዋል።

ይሁን እንጂ የክልሉ አርሶ አደር ለዘመናት ከባህላዊ አሰራር መውጣት ባለመቻላሉ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ ቆይቷል።

አሁን እየመጣ ባለው ሀገራዊ ለውጥ አርሶ አደሩን ወደ ዘመናዊ ግብርና በማሸጋገር ኢኮኖሚ የሚኖረውን ድርሻና ተጠቃሚኑትን ለማሳደግ መንግስት ትኩረት መስጠቱን አመልክተዋል።

“አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የአመራረት ዘይቤውን ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት የምሁራን ሚና የጎላ መሆን እንዳለበት የክልሉ መንግስት ያምናል” ብለዋል።

ምሁራን  በእውቀታቸው ጥናትና ምርምር በማድረግ አርሶ አደሩ ወደ ገበያ ተኮር አምራችነት እንዲለወጥ የሚደረገውን ርብርብ መደገፍ  እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሁለት ቀናት ውይይታቸውም የሚደርሱባቸውን ግኝቶችና ድምዳሜዎች የክልሉ መንግስት ተቀብሎ ወደ አርሶ አደሩ በማውረድ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ አራት ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን በዚህም ግብርናውን ትራንስፎርም በሚያደርጉ ሳይንሳዊና ዘመናዊ እውቀቶችን ለማዳበር ምክክር እንደሚደረግ ታውቋል። (ኢዜአ)