የፋብሪካው ህልውና አደጋ ላይ ነው-ሰራተኞች፤ የሰራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራን ነው- አስተዳደሩ

የሰበታ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ሰራተኞች የፋብሪካው ህልውና አደጋ ላይ ነው ሲሉ የፋብሪካው አስተዳደር በኩሉ የሰራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራ እንደሆነ ገለጸ፡፡

ፋብሪካው አሁን ላይ ምርቱ ተፈላጊ ቢሆንም እያመረተ አለመሆኑንና ቀደም ሲል የተመረተውም እየተደፋ እንደሆነ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡ ተረፈምርቱም ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲጠቀሙበት የሚሰጥ ቢሆንም አሁን መቋረጡን ሰራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የማስታወቂያ ባነሮችን በመገንጠል ሰብስቦ ማስቀመጡ ማምረት ማቋረጡን የሚያሳይ ነው ብለዋል ሰራተኞቹ፡፡

ጥቅማጥቅሞቻቸው እንደማይከበሩ እና ድርጅቱ ሰራተኞችን በተቋሙ ጉዳይ ለማወያየት ፍላጎት እንደሌለውም ሰራተኞቹ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በበኩሉ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ምርት የማቋረጥ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለውና የማምረት አቅሙን እያሳደገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት በፋብሪካው የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ያየራድ አባቴ ድርጅቱ ፋብሪካውን ለመዝጋት እንቅስቃሴ ጀምሯል የተባለውን መረጃ መሠረተቢስ ነው ብለውታል፡፡

ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢ ያሉ ባነሮችን መሰብሰቡ ጊዜ ያለፈባቸው በመሆኑ በአዲስ ለመተካት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ፋብሪካው በቀጣይ የሰራተኛውን ጥቅም የበለጠ ለማስጠበቅ እየሰራ እንደሆነ አቶ ያየራድ አክለው ገልጸዋል፡፡