የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እሁድ ይመረቃል

በአዲስ አበባ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የፊታችን እሁድ በይፋ ይመረቃል።

ግንባታው ጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም. የተጀመረውና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ በ37 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ፕሮጀክት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከሳምንት በፊት በሙከራ ደረጃ ኃይል እያመነጨ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በአማካይ በዓመት 185 ጊጋ ዋት የሃይል ምርት እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ደረጃ በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነም አንስተዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተደረሰው ስምምነት ከከተማዋ ከሚወጣው 1 ሺህ 400 ቶን ቆሻሻ ለሃይል አቅርቦት ምንጭነት እንደሚውልም አመልክተዋል።

የረጲ ደረቅ ቆሻሻን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በትብብር እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታው በቆየባቸው ሶስት ዓመታት ለ 1 ሺህ 300 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ እድል እንደፈጠረም ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ላይ 286 የውጭ አገራት ዜጎች በግንባታው ላይ እንደተሳተፉና ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር እንደሰጡም ነው አቶ ምስክር የተናገሩት።

ከሃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት ለመውሰድ የማስተላለፊያ መስመሮች በሚያልፍበት ቦታ የነበሩ መኖሪያ ቤቶችንና ሌሎች ንብረቶችን ለማንሳት የወሰደው ጊዜ፣ የቦታ ርክክብና ግንባታውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ እቃዎች ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ያለው ሂደት እንዲሁም ፕሮጀክቱን ከሚሰራው ስራ ተቋራጭ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ጋርም የተፈጠሮ የነበረው አለመግባባት የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሚፈለገው ጊዜ ሃይል ማመንጨት እንዳይጀምር ምክንያቶች እንደሆኑም ታውቀዋል።

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከአካባቢ ተጽእኖ ነጻ የሆነና ኢትዮጵያ ታዳሽና አረንጓዴ ሃይል ለማግኘት የምታከናውናቸው እንቅስቃሴዎች አካል አንደሆነም አስገንዝበዋል።

ፕሮጀክቱ ከሃይል ማመንጫነቱ ባለፈ ለስራው የሚውለው ቆሻሻ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ ጽዱና አረንጓዴ እንድትሆን የማድረግ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዋና ተቋራጭነት የእንግሊዝና የአይስላንድ ኩባንያ የሆነው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ፣ በንዑስ ተቋራጭነት ደግሞ የቻይናው ሲኤንኤኢሲ (CNAEC) የተሳተፉ ሲሆን የዴንማርኩ ራምቦል የተባለው ድርጅትም በአማካሪነት ሰርተዋል። (ኢዜአ)