የአገሪቷን የቡና ምርት ከችግሮች ለማላቀቅ ሁሉም በጋራ ሊሰራ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ

የቡና ምርት ከግብይት ችግሮች ተላቆ ዘርፉ ለአገሪቷ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እንዲያመነጭ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት “የቡና ልማት ግብይት፣ እድል፣ ዋና ዋና ማነቆዎችና የመፍትሄ አማራጮች” በሚል ርዕስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የዘርፉን ስራ የሚሰሩ መንግስታዊ የስራ ኃላፊዎች፣ የቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ማሕበራት ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የማህበራቱ ተወካዮች ዘርፉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለ30 ሚሊዮን ሰዎች መተዳደሪያ ቢሆንም አሁንም “በችግሮች የተተበተበ ነው” ብለዋል።

ለዚህ እንደ ዋና ችግሮች ሊጠቀሱ የሚችሉ የቡና ህገ ወጥ ንግድ፣ እሴት ያለ መጨመር፣ ቡናን በዝቅተኛ ዋጋ መሸጥና ዘርፉን በአግባቡ ያለማስተዋወቅ ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው ተብለዋል።

የቡና ጉዳይ ማዕከላዊ በሆነ መልኩ በአንድ መስሪያ ቤት አለመመራቱም ሌላው ችግር መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የቡና አምራቾች ለተለያዩ የጸጥታ ችግሮች መጋለጣቸው ሌላው ስጋት መሆኑ ተገልጿል።

በተለይ ደግሞ ዘርፉ ለ15 ዓመታት የአንድ ኩንታል ጭማሪ እድገት እንኳን አለማሳየቱ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሰብሰብ ብለው በኩባንያ መልክ ቢንቀሳቀሱ የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘም መንግስት የሚሰራው ስራ እንዳለ ሆኖ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸው ባለበት አካባቢ ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል ያሉ ሲሆን የዘርፉ አንቀሳቃሳሾች ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችም የኢትዮጵያ ቡና መለያ እንዲያዘጋጁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ሰንዝረዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ የቡና ምርት ከግብይት ጀምሮ ውስብስብ ችግሮች ስላሉበት መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ጠይቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የቡና ጉዳይ ማዕከላዊ በሆነ መልኩ በአንድ መስሪያ ቤት የሚመራ ሳይሆን በስድስት መስሪያ ቤቶች ለዘርፉ አንቀሳቃሾች አገልግሎት መስጠቱ ችግር እንደሆነ አንስተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአገሪቱ ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የቡና አምራቾች ለተለያዩ የጸጥታ ችግሮች መጋለጣቸውም ሌላው ስጋት መሆኑ ተገልጿል።

ዘርፉ ራሱን በማስተዋወቅ ረገድ አሁንም ገና መሆኑና የኢትዮጵያን ቡና የሚያስተዋውቅ መለያ አለመኖርም እንደ ችግር ተነስቷል።

በውይይቱ ወቅት መነሻ ገለጻ ያቀረቡት የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ዘርፉ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለ30 ሚሊዮን ሰዎች መተዳደሪያ፤ 40 በመቶ ገደማ የሚሆን የውጭ ምንዛሪም ማግኛ ነው።

 በአማካይ በየዓመቱ የቡናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት ገቢ 25 በመቶውን ድርሻ እንደሚያዝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ችግሮቹ ይፈቱ ዘንድ ከሁሉም በላይ ምርታማነትን ማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን መጠቀምና እሴት መጨመር በዋናነት ይተግበሩ ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከላከችው 238 ሺህ 465 ሜትሪክ ቶን ቡና 838 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን ይህም ከ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት አንጻር የ44 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

ምርቱ ከ60 በላይ ለሚሆኑ አገራት የተላከ ሲሆን ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያና አሜሪካ ዋነኛ መዳረሻዎች ናቸው። (ኢዜአ)