የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማርካት ከዘርፉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅ ፕ/ት ዶክተር ሙላቱ ገለጹ

የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማርካት የኤሌክትሪክ ሃይልና አቅርቦትን በማመጣጠን ሂደት ከዘርፉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡ 

በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የምረቃ ስነ-ስርዓት በትላንትናው እለት ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ እነዚህን መሰል ፕሮጀክቶችና የሃይል ማመንጫዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት የህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ማርካት ይገባል፡፡

ባለፉት ዓመታት በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ዘርፍ የተሰራው ስራ ለኢኮኖሚ እድገቱ ወሳኝ ሚና እንደነበረው የገለጹት ፕሬዝዳንት  ዶክተር ሙላቱ ስራውን በማስቀጠል የዜጎችን የሃይል ፍላጎት ማሟላት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

በሚቀጥሉት ሰባት አመታት <<ብርሃን ለሁሉም>> የሚለውን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት ስራው ላይም መንግስት ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይሄን ተግባራዊ ለማድረግም በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ማሳተፍ እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ  ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሃይል የማመንጨት እምቅ አቅም መኖሩን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በትኩረት እየሰራ እደሚገኝ ነው የተናገሩት።

የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሲሆን ወጪው ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ሲሆን የካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ በዋና ስራ ተቃራጭነት እንዲሁም የቻይናው ሲንኢኢና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በሰብ ኮንትራክተርነት ተሳትፈዋል።

ከአምስት አመት በፊት በ2006 ዓ ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በአመት በአማካይ 185 ጊጋ ዋት ያመነጫል፡፡

ኃይል ለማመንጨት በቀን 1 ሺህ 400 ቶን ደረቅ ቆሻሻ በግብዓትነት ይጠቀማል በዚህም 185 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ፐር ሃወር ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

ከሃይል ማመንጨት ጎን ለጎንም በአዲስ አበባ ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በማዘምንም ትልቅ ጠቀሜታ አለው ተብሏል። (ኢዜአ)