ከስድስት ወራት በኋላ ሁሉም የስኳር ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጠናቀቃሉ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ

ከስድስት ወራት በኋላ የሁሉም የስኳር ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህርዳር ከተማ ከብአዴን አመራሮች ጋር ባደረጉት ምክክር ግንባታቸው በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ የነበሩ የስኳር ፕሮጀክቶች አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 9 ወራት የተሻለ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የተሻለ መግባባት ለመፍጠርም ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የነበረውን ግንኙነት የማስተካከልና በኃይማኖቶች ውስጥ የነበረውን መከፋፈል የማጥፋት ስኬታማ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ ረገድም የውጭ ምንዛሬ በቤታቸው ያከማቹ ዜጎች ወደ ባንክ እንዲያስገቡ በተጠየቀው መሠረት በሁለት ሳምንታት ብቻ እስከ 130 ሚሊየን ዶላር በባንኮች መመንዘሩን የገለጹት ዶክተር አብይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጡት መልካም ለውጦች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ትክክለኛ የአመራር ስልትን ለመተግበር አመራሮች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ (ምንጭ፤ አማሃራ መገነኛ ብዙሐን ኤጄንሲ)