የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየተመዘበ ላለው ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው

የአገሪቱ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር  እንዲሁም ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድልን በመፍጠር እየተመዘበ ያለውን አገራዊ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ቀጣይነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

 ኮሚሽኑ በ2010 በጀት አመት ኢንቨስትመንት ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረውን ድርሻ እንዲጎለብት ለማድረግ የሚያስችል አመርቂ ተግባር ማከናወኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የሃገሪቱን የኢንቨስትመንት ዕድሎች በሚያስተዋውቁ ዓለም ዓቀፍ ፎረሞችና የንግድ ትርዒቶች ላይ በመሳተፍ በሃገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና ምቹ ሁኔታዎች የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱም ተጠቁሟል፡፡

በበጀት ዓመቱ  ሃገሪቱ ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡

ኢንቨስትመንትን ከመሳብ እንዲሁም የሃገርና የውጭ ባለሃብቶችን ከመደገፍ ባሻገር የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በማስፋፋት አመርቂ ተግባር ተከናውኗል፡፡

ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች የተሰሩ ከመሆኑም በላይ ኮሚሽኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ወደ ሃገሪቱ ገብተው ስራ ለጀመሩ ባለሃብቶችም የተለያዩ ድጋፎች አድርጓል፡፡

በበጀት አመቱ በኢንቨስትመንት ምንጭነት ተቀዳሚ የሆኑ አገራትና ባለሃብቶች የተለዩ ሲሆን በቀዳሚነት ቻይና በሁለተኝነት የህንድና ቱርክ ባለሃብቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በበጀት አመቱ 5 ነጥብ07 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳትፎ  ለማድረግ ያሰቡ 275 የውጭ ባለሃብቶችና ኩባንያዎችም የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተዋል፡፡

እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማበረታቻ በዋና መስሪያ ቤትና በየፓርኮች መፍቀድን በተመለከተ በበጀት አመቱ 49 ቢሊዮን ብር ግምት የኢንቮይስ ዋጋ ላላቸው 8 ሺህ 36 የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማበረታቻ ጥያቄዎች ፈቃድ ለመስጠት ተችሏል፡፡

ካፒታላቸው 16 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሆኑ 198 ፕሮጄክቶችን ወደ ማምረት ወይም አገልግሎት መስጠት የተሸጋገሩ ሲሆን ከ57 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 252 ፕሮጄክቶች ወደ ትግበራ ተሸጋግረዋል፡፡

ሃገሪቱ ኢንቨስትመንትን በመሳና በማስተዋወቅ እንዲሁም ውጤታማ የፖሊሲና የአሠራር ማሻሻያዎችን በመተግበር ላስመዘገበችው ላቅ ያለ የኢንቨስትመንት ፍሰት የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የAIM 2018 ሶስት ሽልማቶች ባለቤት መሆኗም በመግለጫው ተካቷል ፡፡