ከ5 ሚሊየን ብር በላይና በርካታ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

5 ሚሊየን ብር በላይና በርካታ የውጭ ሀገር ገንዘቦች በቁጥጥር ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት ገንዘቦችም 5 ሚሊየን 466 ሺህ 632 ብር፣ 4 ሺህ 16 እንግሊዝ ፓውንድ፣ 56 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ 2 ሺህ 70 ዩሮ፣ 6 ሺህ 505 ድሪሃም ናቸው።

እንዲሁም በርካታ የደቡብ አፍሪካ ራንድ፣ የቱርክ ሊሬ፣ ጅቡቲና የሶማሊያ ሺልንግ እንዲሁም የማሊ ፍራንክ መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

በኮሚሽኑ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይናስ ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር ደበበ ድጋፍ፥ ገንዘቦቹን በመያዝ በጋንዲ ሆስፒታል፣ ኢትዮጵያ ሆቴልና ሌሎች አካባቢዎች በህገወጥ መንገድ ሲዘረዝሩ እንደተያዙ አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ህገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ሲካሄድባቸው የነበሩት30 በላይ የሚደርሱ የንግድ ሱቆች ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር እንዲታሸጉ መደረጉን ገልፀዋል።  

የንግድ ቤቶቹ የታሸጉት በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሚመራ ግብረ ኃይል ሲሆን፥ ፖሊስ ከትናንት ጀምሮ ባካሄደው ድንገተኛ ክትትል እና ፍተሻ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

የንግድ ቤቶቹ የታሸጉበት ምክንያትም በህጋዊ የንግድ ፍቃድ ህገ ወጥ ተግባር በመፈፀማቸው ነው የተባለ ሲሆን፥ ተግባሩም ህገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ማለትም በህገ ወጥ መንገድ የውጭ ሀገራት ገንዘብን መግዛት እና መሸጥ ድርጊት ነው።

በተጨማሪም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አሜሪካ ጊቢ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እና በቦሌ ክፍለ ከተማ ሁለት አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የሚገኙ የንግድ ሱቆች ናቸው በተደረገው ፍተሻ ተለይተው ታሸገዋል።

በፍተሻው ወቅትም በርካታ የውጭ ሀገራት እና የሀገር ውስጥ ገንዘቦችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል። (ኤፍ..)