የኢንቨስትመንት ቦርድ አለም አቀፍ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ስራ እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ውሳኔ አሳለፈ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠንና ኢንቨስትመንትን እንዲሁም የውጭ ንግድ አፈፃፀምን በበቂ መጠን ለማሳደግ የሚያግዝ የፖሊሲ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፥ የተላለፈው ውሳኔ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር ከሀገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች በሽርክና መስራት የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአምራቹን ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የውጭ ንግድ አፈፃፀምን በበቂ መጠን ለማሳደግ የሎጂስቲክስ እና የጉምሩክ አሠራሮችን ማሻሻል እንደሚገባ የተገለፀ ቢሆንም እስካሁን በዘርፉ ይህ ነው የሚባል ጉልህ መሻሻል አልታየም ብሏል ቦርዱ በመግለጫው።

በአጠቃላይ ዘርፉ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅ ብዙ ርቀት መጓዝ የሚኖርበት ሲሆን፥ ለዚህም እንደማሳያ የሚሆነው የሀገሪቱ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪና የጉምሩክ ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ አፈፃፀም ላይ መገኘቱ ነው።

ይህንንም ለማስተካከልና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተያዙ እቅዶችን ወደ መሬት ለማውረድ የብሔራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ፀድቋል። 

ከዚህም ጎን ለጎን ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች በመለየት አቅጣጫዎችን የሚጠቁም ጥናት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በኮሚሽኑ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

ዘርፉ ካሉበት የተለያዩ ውስንነቶች መካከል በዘርፉ የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ በመገደቡ፣ በወጪ ንግድና በማምረቻ ኢንዱስትሪ የስራ ዘርፍ እና በሌሎች የገቢና ወጭ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በዘርፉ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት
ማግኘት አለመቻላቸው የሚጠቀስ ነው።

በተለይ አለም አቀፍ አምራች ድርጅቶች በሌሎች ተወዳዳሪ በሆኑ ሃገራት በቀላሉ የሚጠቀሙባቸውን አገልግሎቶች በሃገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው በአለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸውን እየጎዳው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል።

ስለዚህም ሀገሪቱ ቴክኖሎጂ ተኮርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተለዋዋጭ ከሆነው የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪ ጋር አብራ እንድትጓዝ ለማድረግና ዘርፉ ለሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች እና እራሱን ችሎ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያበረክትበትን አሰራር ለመዘርጋት እንዲያስችል ከተመላከቱት ማሻሻያዎች መካከል አለም አቀፍ ልምድ ያካበቱ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከሃገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብሮ መስራት የሚያስችላቸውን ማሻሻያዎች ማድረግ ነው።

በዚህም የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተወዳዳሪነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማስጠበቅ፣ ብሎም የቴክኖሎጂና የልምድ ልውውጥ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማስቻል የውጭ ባለሃብቶች አናሳ ድርሻ በሚይዙበት መልኩ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ይገኝበታል።

ቦርዱም በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት፣ የቦንድድ መጋዘን፣ የኮንሶሊዴሽንና ዲኮንሶሊዴሽን አገልግሎትን ማቅረብን ጨምሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 270/2005 (እንደተሻሻለው) ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች ብቻ ተከልሎ የነበረውን ዕቃዎችን የማሸግ፣ የማስተላለፍ እና የመርከብ ውክልና አገልግሎቶችን በመስጠት የኢንቨስትመንት መስክ አለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ ያላለፈ አናሳ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ የሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና አብረው መሥራት እንዲችሉ ውሳኔ አስተላልፏል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)