ለስራ እድል ፈጠራ ከተመደበው በጀት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ስራ ላይ መዋሉ ተገለጸ

ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ከተመደበው በጀት ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ስራ ላይ መዋሉ ተገለጸ፡፡

የፌዴራል መንግስት በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች የሚውል 10 ቢሊዮን ብር ለስራ እድል ፈጠራ መመደቡ ይታወሳል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት የሐረሪ ክልል መቶ በመቶ የበጀት እድሉን በአግባቡ የተጠቀመ ሲሆን የአፋር ክልል 40 በመቶ በማከናወን ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳለው በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል 90 በመቶ፣ የአማራ ክልል እና ደሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 80 በመቶ፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች 70 በመቶ አፈጻጸም ያላቸው ሲሆን የትግራይ ክልል ደግሞ 60 በመቶውን ጥቅም ላይ ማዋሉንን አቶ ሀጂ ኢቢሳ ለጋዘጠኞች በሠጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከቀበሌ አንስቶ  በክልል አስተዳደር ተረጋግጦ የሚቀርብለትን የገንዘብ ፍሰት ሪፖርት የሚከታተል ሲሆን በተደጋጋሚም ችግር ያለባቸውን ሪፖርቶች ተመላሽ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በየደረጃው ሀላፊነት ወስዶ በቀጥታ ክትትል የሚያደርግ አካልም ለተቋሙ መረጃ እንዲያቀርብ መደረጉን የገለጹት ዳይሬክተሩ በቀጣይም አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ፈሰስ የሚደረግብት አግባብ አንዳለ የታወቀ ሲሆን የእስካሁኑ ጥቅል አፈፃፀሙ ሲታይ 82 በመቶ መድረሱ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ተቋሙ ከ2009 አንስቶ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ወጪ ቅነሳን መሠረት ያደረገ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲከቱሉ ማድረጉን ተከትሎ በ2010 በጀት አመት 600 ሚሊዮን ብር ከብክነት መትረፉን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በመደበኛና ካፒታል በጀት አጠቃቀም መሻሻል መኖሩን ያነሱት ዳይሬክተሩ 188 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች የወጪ ቁጠባ መመሪያውን እንዲተገብሩት ትዕዛዝ መተላለፉን አንስተዋል፡፡ 

በተጠናቀቀው በጀት አመት ሀገሪቱ 16 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የውጪ እዳ መክፈል እንደቻለች እና በአዲሱ በጀት አመት ደግሞ 22 ቢሊዮን ብር እዳ ለመከፈል እቅድ መያዙን ዳይሬክተሩ አስታውቋል፡፡