የቤንዚን እጥረት በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሽከርካሪዎች ገለጹ

በየጊዜው እያጋጠማቸው ባለው የቤንዚል እጥረት በዕለት ተዕለት ሥራቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን  የደብረ ብርሃን ከተማ  አሽከርካሪዎች ገለጹ።

በከተማው ባለ ሶስት እግር ታክሲ አሽከርካሪዎች እንደገለጹት በቤንዚል እጥረት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመሥጠት ማግኘት የሚገባቸውን ገቢ እያጡ ነው፡፡

ከጥቁር ገበያ ሊትሩን ቤንዚን እስከ 40 ብር በመግዛት መሥራት ቢሞክሩም ከከተማው የታክሲ ትራንስፖርት ታሪፍ አንጻር አዋጭ ባለመሆኑ ተቸግረው እንዳሉም አሽከርካሪዎቹ አመልክቷል።

የኦይል ሊቢያ ቁጥር አንድ ማደያ ተቆጣጣሪ አቶ ንጉሴ ፍልፍሉ ከሁለት ቀናት በፊት 26ሺህ ሊትር ቤንዚል ማስገባታቸውን ተናግረው በሌሎች ማደያዎች ቤንዚል የለም በማለት ሁሉም የባለ ሶስት እግር ታክሲ ባጃጆች ወረፋ እየጠበቁ ይገኛሉ።

አሁን ላይ የቀረ 18 ሺህ ሊትር ቤንዚል ስላለ ተገልጋዮች ተረጋግተው በወረፋቸው ሊሰተናገዱ እንደሚገባ ጠቁመው ተጨማሪ ከጅቡቲ ለማስመጣት መታዘዙንም ገልጸዋል፡፡

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘይኑ አልይ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በከተማው ያሉ አምስት ማደያዎች ፈጥነው ቤንዚል እንዲያስገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ቤንዚን ማስመጣት እየቻሉ አለግባብ ችላ በሚሉ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

አንድ ሺህ 375 ሊትር ቤንዚል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ተገኝቶ መወረሱንና በዚህ ላይ ተሳትፎ በነበራቸው አራት ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጽህፈት ቤቱ አስታውሷል፡፡