የጎዳና ንግድ ላይ የተሠማሩ ከ6ሺህ በላይ ነጋዴዎች ወደ መደበኛ ንግድ መግባታቸውን ቢሮው አስታወቀ

መደበኛ ባልሆነ የጎዳና ንግድ ተሰማርተው የነበሩ ከስድስት ሺህ በላይ ነጋዴዎች ወደ መደበኛ ንግድ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለፀ።

 

ቢሮው ወደ መደበኛ ንግድ ያልገቡ የጎዳና ነጋዴዎችን ህጋዊ ለማድረግ የመስሪያ ቦታ ማዘጋጀቱንም አስታውቋል።

 

የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የንግድ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መስፍን አሰፋ ንግድ ቢሮው ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ባደረገው ምዝገባ 24 ሺህ 778 መደበኛ ያልሆኑ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

 

ከነዚህ ውስጥም 6 ሺህ 502 ነጋዴዎችን በመመዝገብና የንግድ መለያ ቁጥር በመስጠት ወደ መደበኛ ንግድ ማስገባቱን ገልጸዋል።

 

ቀሪዎቹም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓም ድረስ የነዋሪነት መታወቂያ እና የስራ አጥነት ማስረጃ በመያዝ በየወረዳቸው በመመዝገብ ህጋዊ ነጋዴ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

 

ቅድሚያ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚሰጥ ቢሆንም ከክልሎች ለመጡ ነጋዴዎችም ምዝገባና የስራ ቦታ እደላ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

 

ወደ መደበኛ ንግድ መግባታቸው ተመዝግበው ግብር ለመክፈል እና ህገ-ወጥነትን ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል።