ጠ/ሚ አብይ አህመድ የቡልቡላና ሻሸመኔ ከተማ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገበኙ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቡልቡላና ሻሸመኔ ከተማ የሚገኙ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮጀክቶቹንን አጠቃላይ የስራ አፈፃፀም ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ጋር በመሆን ነው የጎበኙት።

የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርና ምርቶችንና የእንስሳት ተዋዕፆዎችን በማቀናበር ወደ ውጭ የሚልክ ነው ።

በወላቡ ኮንስትራክሽን ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ግንባታው የተጀመረው ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፉ ግንባታ 53 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ በዋናነት ያተኮረው ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰራተኞች እንዳሉት ተነግሯል።

ፓርኩ በ260 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑ ተገልጿል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘውን የግብርና ተቀናጀ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ጎብኝተዋል።

በወላቡ ኮንስትራክሽን ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው ማዕከሉ ሰባት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ አምራቾችን ከአርሶ አደሩ ጋር ለማገናኘት ያስችላል ተብሏል።

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአግሮ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሆነ አርሶ አደር ላለባት አዋጭ የኢኮኖሚ እድገት ዘርፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንዲሁም ሀገሪቱ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ያላት በመሆኑ የግብርና ኢንዱስትሪ ዘረፍ የስራ እድል በመፍጠር ስራ አጥነትን ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።

ግንባታውን በጥቂት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን፥ ፍራፍሬ፣ ወተት፣ ማር እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደሩ የሚረከብ ነው ተብሏል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)