ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአይ.ኤም.ኤፍ ልኡካን ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ልዑካንን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ዓመታዊ ኢኮኖሚ ግምገማ ለማድረግ አዲስ አበባ ከሚገኘው የተቋሙ ልኡክ ጋር በትላንትናው እለት ተገናኝተው ተወያይተዋል።

በቆይታቸውም የአይ.ኤም.ኤፍ ልኡካን የኢትዮጵያን ዓመታዊ ኢኮኖሚ ግምገማ ውጤት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስረክበዋል።

በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ፈጣን እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር መሆኑን መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ልዩ ሀላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም ተከስተ እና ከብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ጋር ተገናኝቶ ውይይት ማድረጉም ይታወሳል።

በተጨማሪም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የፊስካል ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት የሥራ ኃላፊዎችም ጋር በ2010 የፊሲካል ፖሊሲ አፈጻጸምና በ2011 በጀት ላይ የመጀመሪያውን ስብሰባው አካሄዷል፡፡

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ልዑክ የሀገሪቱን የአውሮፓውያኑ የ2018 ዓመታዊ ኢኮኖሚ ግምገማ ለማድረግ ከሳምንታት በፊት ነበር አዲስ አበባ የገባው።

በሚስተር ጁሊዮ ኤስኮላኖ የሚመራው ይህ ልዑክ በኢትዮጵያ ቆይታውም በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በፊሲካል ፖሊሲ፣ በገንዘብና ፋይናንስ ዘርፍ እና በውጭ ዘርፍ ዙሪያ አፈጻጸሞችን ገምግሟል።