የኢትዮ-ሳዑዲ የኢንቨስትመንት ጉባዔ ተካሄደ

የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት ጉባዔ በኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በዛሬው ዕለት በሪያድ ከተማ ተካሂደ።

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል፦  በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በኢንቨስትመንት እድሎች፣ በኢንቨስትመንት ዘርፎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና ልማት እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ስለሚያገኙት የመንግስት ድጋፍ እና አጠቃላይ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጭ ሃሳቦች ላይም ሚኒስትር ዲኤታው  ማብራሪያ አቅርበዋል።

እንዲሁም  ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ ላይ መሆኗን፣ ሰፋፊ የመሰረተ-ልማት ግንባታ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለች ሀገር እንደሆነች የገለፁ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም አገሪቱ ያላትን የኢኮኖሚ ይዘት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የማምረቻ ኢንዱስትሪ ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታና ልማት ውስጥ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

የውጭ ባለሃብቶች በተለይም የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች በእነዚህ የኢንዱስትሪ ልማት ግንባታዎች፣ በኃይል ማመንጨት፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ እና በጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ጉባዔ ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ባለሃብቶችና የኢንቨስትመንት ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ በመልካም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ ላይ እንደሆነችና  በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ተሳተፊዎቹ ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን ያነሱ ሲሆን፥ ሚኒስትር ዴኤታው በበኩላቸው መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን ለማገዝና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)