በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ያፈሩትን ኃብት ይዘው ወደአገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ይመቻቻል ተባለ

በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን  ያፈሩትን ኃብት ይዘው ወደ ሀገራቸው በመግባት የተረጋጋ ህይወት መምራት የሚችሉበትን አሰራር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

በሳውዲ ዓረቢያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የተሳተፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን  በሪያድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ጋርም ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ያፈሩትን ሃብት ይዘው ያለ ምንም ችግር ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ሁኔታዎች እንዲያመቻቹላቸው ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ዜጎች በውጭ አገር ሲኖሩ ያፈሩትን ኃብትና ጥሪት ወደ አገራቸው ይዘው እንዲገቡ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በሚመለከተቻው አካላት በመከናወን ላይ ነው።

ኢትዮጵያዊያኑ ኃብትና ንብረታቸውን ይዘው ጉዳትና ችግር ሳይገጥማቸው ወደ አገር ቤት መመለስ የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ የሚወሰደው አርምጃ ለሌላ ህገ ወጥ ተግባር በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ገልፀዋል።

በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር፣ ገቢዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት አንድ ላይ ሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝግጅቱን ጨርሰው ለመንግስትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቅረብ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው ለአደጋ እንዳይጋለጡ፣ ስለሚሄዱበት አገርም ሆነ ስለሚሰማሩበት የስራ መስክ በቂ መረጃና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እንደሚከናወንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በህጋዊም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር የወጣው ዜጋ ለሚኖርበት አገር እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በእኩል ዓይን የሚታዩ መሆናቸውን ጠቅሰው  በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና አደጋ እንዳይደርስባቸው የመከላከል ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን በበኩላቸው መንግስት መብታቸው እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ የሚሰሩባቸው ቦታዎች እንዲታወቁ፣ ወደ አገራቸው ሲገቡ ማረፊያ የሚያገኙበትና ያፈሩትን ሃብት ይዘው ያለ ምንም ችግር ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ሁኔታዎች እንዲያመቻቹላቸው ጠይቀዋል። (ኢዜአ)