ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍና ብድር አፀደቀ

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ1 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍና ብድር ማጽደቁን አስታወቀ ። 

የዓለም ባንክ  ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ በአጠቃላይ 1ነጥብ2  ቢሊዮን ዶላር  ድጋፍና ብድሩን  ማጽደቁን  ገልጿል።

ባንኩ እንደገለጸው 600 ሚሊየን ዶላሩ በድጋፍ መልክ የሚሠጥ ሲሆን፥ 600 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ብድር ነው።

ባንኩ ድጋፍና ብድሩን  ለመሥጠት  ያቀደው የኢትዮጵያ መንግስት ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማድረጉን እንዲሁም የፖለቲካ ምህደሩን ማስፋቱ ቀጠናዊ መረጋጋት እንዲመጣ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑንም ለድጋፉ ትልቅ አስተዋጽኦ  ማድረጉ ተጠቅሷል።

 ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሻሻዎች ማድረጉን እና ይህ ጥረቱም እንዲሳካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ  ነው  ባንኩ እንደዚህ አይነት ምላሽ  መሥጠቱም ተመልክቷል።

 ባንኩ ያደረገው የገንዘብ ድጋፉና ብድሩ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፏን እና የኢንቨስትመንት ምህዳሯ ላይ ማሻሻያ እንድታደርግ  የሚረዳ መሆኑን ተጠቅሷል  ። (ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)