የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የ123 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ

የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ለተለያዩ አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚውል የ123 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ ።   

ባንኩ ያፀደቀው ድጋፍ እስከፈረንጆቹ 2020 ድረስ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ለሚተገበረው ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ነው ተብሏል።

ባንኩ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና፣ የትምህርትና የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የንጽህና አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚያደርገው ድጋፍ አካል መሆኑም ተገልጿል።

ድጋፉ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን፥ ለሰብዓዊ ልማት እና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ይውላልም ነው የተባለው።    

የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ለመሠረታዊ አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮግራሞች የሚውል  ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት እኤአ በ2015 ማፅደቁ ይታወሳል።

ድጋፉ በአብዛኛው በገጠር አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፥ በአፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮችም ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በኢትዮጵያ የመሠረታዊ አገልግሎትን ለማሻሻል በተካሄደው ፕሮጀክት በትምህርት፣ ጤና እና በንጹህ መጠጥ ውሃና ንጽህና አገልግሎት በርካታ መሻሻሎች ታይተዋል።

በትምህርቱ ዘርፍ ወደ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገቡ ተማሪዎች በፈረንጆቹ 2006 ከነበረበት 77 ነጥብ 5 በመቶ በ2016 ወደ 99 በመቶ ሲያድግ፥ የእናቶችና ህጻናት ሞትንም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።    

እኤአ በ2006 ከ1 ሺህ ህጻናት 72 የነበረው የሞት መጠን በ2016 ከ1 ሺህ ህጻናት ወደ 20 ዝቅ ማለት ችሏል ።

ከዚህ ባለፈም በገጠር ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን  እኤአ 2006 ከነበረበት 46 በመቶ በ2017 መጨረሻ ወደ 74 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያን አበረታች ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብና አመርቂ የመዋቅር ሽግግር በማድረግ ላይ የምትገኝ ሃገር በሚል ዝርዝር አካቷታል። (ምንጭ: አፍሪካ ልማት ባንክ )