ከዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክና ዲሞክራቲክ ኮንጎ የመጡ ልዑካን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ጎበኙ

ከዚምባቡዌ፣ ሞዛምቢክ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ የመጡ ልዑካን የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታ ጎበኙ፡፡ የግድቡን የግንባታ ሂደት  ከተመለከቱ በኋላ እንደገለፁት ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በህዝቦች ተሳትፎ የሚከናወን መሆኑ የሚያኮራ እና የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሌሎች ሀገራት አስተማሪ ፕሮጀክት መሆኑን  ጎብኝዎች ገልፀዋል፡፡

ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የመጡት ሙዙንጉ ያከሉ ህዝቡ በግድቡ ግንባታ ላይ መሳተፉ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥርና አስተማማኝ የፋይናንስ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዚምባቡዌ የኃይልና የልማት ሚኒስትር ኢንጂነር ቤንሰን ፒያርቲ በበኩላቸው ቀደም ሲል መሰል ፕሮጀክትን አፍሪካውያን ሊገነቡ እንደማይችሉ ነበር የሚታሰበው፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ የተመለከትነው አፍሪካውያን ከተባበርን ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም መገንባት እንደምንችል ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

(ምንጭ፡-ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት)