የኦሮሚያ ልማት ተነሽዎች ጉዳይ ኤጀንሲ የልማት ተነሽዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

የኦሮሚያ ልማት ተነሽዎች ጉዳይ ኤጀንሲ የልማት ተነሽዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ኤጀንሲው ትላንትና በሠጠው መግለጫ በተያዘው በጀት ዓመት ለልማት ተነሽዎች 4 ቢሊየን ብር የካሳ ክፍያ ለመክፈል እቅድ መያዙን አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም በልማት ምክንያት ከቤትና የመሬት ይዞታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች አስተማማኝና ዘላቂ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

የከተሞች የካሳ ክፍያ ታሪፍ መሻሻሉንና ለ5 ሺህ 820 አባወራ የልማት ተነሽዎች የመኖሪያ ቤት መስጠቱንም ኤጀንሲው አስታውቋል።

ለ6 ሺህ 375 አባዎራ የልማት ተነሽዎች የመኖሪያ ቤት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ያለው ኤጄንሲው 15 ሺህ 901 የልማት ተነሽዎችን በዱከም፣ ሰበታና ለገጣፎ ፥ በልብስ ስፌት፣ በከተማ ግብርና፣ በገበያ ማዕከሎችና በማምረቻ ሼዶች በማሰማራት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ኤጄንሲው ገልጿል።

በልማት ድርጅቶች፣ በኢንቨስትመንት፣ በግልና በጋራ ኢንተርፕራይዞች ውስጥም ለ10 ሺህ 723 የልማት ተነሽዎች የስራ እድል መፈጠሩን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።