በዘንድሮ የሩብ በጀት ዓመት ከ1ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የስትራቴጂክ ግዥዎች መፈጸማቸው ተገለጸ

የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በዘንድሮ የሩብ በጀት አመት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የስትራቴጂክ ግዥዎችን መፈጸሙን አስታወቀ ።

አገልግሎቱ በተጨማሪ ያገለገሉ ንብረቶችን በመሸጥ ከ 22 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ  ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡  

መሥሪያ ቤቱ የሩብ አመት አፈጻጸሙን በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

 አገልግሎቱ ከመንግሰት ተቋማትና ልማት ድርጅቶች በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ነው ያገለገሉ ንብረቶችን በመሸጥ ከ 22 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ መንግስተ ካዝና ገቢ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

መሥሪያ ቤቱ የበጀት አመቱን ሩብ አመት አፈጻጸም በሚመለከት ከፌደራል ባለበጀት መንግስት መስሪያ ቤቶች እና አቅራቢዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ፣ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የማዕቀፍ ስምምነት አቅራቢ ድርጅት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በመስሪያ ቤቱ እያከናወነ ባለው የግዢና ንብረት ማስወገድ ስራዎች ላይ የሚታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን አንስተዋል፡

የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች እንደገለጹት ከተጠቃሚ መስሪያ ቤቶች ፍላጎት መሰብሰብና ማደራጀት፣ የጥራት ናሙና ፍተሻ ማስደረግ፣ ጨረታ መገምገምና በግምገማው ውጤቱ ላይ ተጫራቾች የሚያቀርቡትን ቅሬታ ማስተናገድ የግዢ ሂደቱን ከሚያጓትቱ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ የተሻለ የአሠራር ሥርአት ለመዘርጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

መሥሪያ ቤቱ ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በሶስት አመታት ውስጥ በ38 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የተለያዩ ግዥዎች ማከናወኑ የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ እስካሁን ከ74 ቢሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙ ታውቋል፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የፌደራል የመንግስት ግዥ አፈጻጸምንና ንብረት ማስወገድን እንዲያስፈጽም በአዋጅ የተቋቋመ መንግስታዊ መስሪያ ቤት ነው፡፡