በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግር ማነቆ እየሆነ ነው

ግንባታቸው ተጠናቀው ወደ ሥራ ከገቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግር ማነቆ ሆኖ እንዳስቸገረው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎቹ ለልማት የሚነሱ ነዋሪዎች በዘላቂነት ህይወታቸው የሚሻሻልበትን ተግባራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል።  

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ 11 የኢንዱስትሪ ፖርኮችን ለማልማት እየሰራ ሲሆን አምስቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል።

በሚቀጥሉት ጊዜያት ደግሞ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለውን የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ አራት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።  

በቀጣይ ሶስት ወራት ወደ ስራ የሚገቡት የደብረብርሃን፣ የባህርዳር፣ የቂሊንጦና ቦሌለሚ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በጥራትና በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

ይሁንና በፓርኮቹ የሥራ እንቅሰቃሴ ላይ ማነቆ ከሆኑት የኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦት ባሻገር የሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግር ትልቅ ተግዳሮት እየሆነና በየወቅቱ ሠራተኞች ከሥራ እንዲለቁ እያስገደደ መሆኑን አመልክተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላትና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመነጋገር ላይ ሲሆን በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሙከራ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ይህም የፓርኩ ሰራተኞች የኪራይ ቤት እንዲያገኙ፣ መንግስትና የግሉ ባለሃብት በአጋርነት ቤት እንዲገነቡ፣ ኢንቨስተሮች የመኖሪያ ቤት እንዲያዘጋጁ ማድረግና ከተማ አስተዳደሮች ለቤት አቅርቦት የሚሆን በጀት መድበው እንዲሰሩ የማስቻልና የመግፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ወይዘሪት ለሊሴ ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለልማት የሚነሱ ነዋሪዎች በዘላቂነት ህይወታቸውን የሚያሻሽሉባቸው ተግባራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛል።

በተለይም የልማት ተነሺዎች ለልማት በሚነሱበት ጊዜ በግንባታዎች ውስጥ ቅድሚያ የሥራ እድል እንዲያገኙ፣ በግንባታ ወቅትና ግንባታቸው ከተጠናቀቀ በኋላ የተለያዩ የሥራ እድሎች እንዲፈጠርላቸው የሚያደርግ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

ሥራው ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በ2009 ዓ.ም የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት የተጠቃለለ ሪፖርት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የማልማትና የማስተዳደር ስራዎች አፈጻጸም ላይ በሰጠው አስተያየት በቦሌ ለሚ ቁጥር አንድና ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተቀጥረው ለሚሰሩ ሰራተኞች መኖሪያ ቤት ታሳቢ ያልተደረገ መሆኑን ማመልከቱ ይታወሳል።

በአገሪቷ 11 የኢንዱስትሪ ፖርኮች እየለሙ ሲሆን አምስቱ ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል።

በቀጣይ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እንደተጠናቀቀ ሲሆን አራቱ ደግሞ በመጪዎቹ ሶስት ወራት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።(ኢዜአ)