በኩታ ገጠም ማሳ በመዝራት ምርታማነታቸውን እያሳደጉ እንደሆነ የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

በኩታ ገጠም ማሳ በመዝራትና የግብርና ግብዓት በመጠቀም በምርትና ምርታማነታቸው ላይ ውጤት እያመጡ እንደሆነ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን የኤጀርሳ ለፎ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

አርሶ አደሮቹ ይህንን ያሉት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጣይባ ሀሰን የተመራ ቡድን በወረዳው የሚገኙ በኩታ ገጠም ማሳ የተዘሩ የተለያዩ ሰብሎችን፣ የአርሶ አደር ማሠልጠኛ እና ምርት ማላመድ ሥራዎችን በጎበኙበት ወቅት ነው።

 

በግብርና ባለሙያዎች በሚሠጣቸው ሥልጠና መሠረት የተለያዩ የግብርና ምርት ማሻሻያ ዘዴዎችን መተግበራቸው ውጤታማ እያደረጋቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከዚህ በፊት በሄክታር 26 ኩንታል ብቻ ያገኙ የነበሩት አርሶ አደሮቹ እስከ 58 ኩንታል የሚደርስ የስንዴ ምርት እያገኙ እንደመጡ ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ዓመት በወረዳው ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምባይነር የስንዴ ምርት መሰብሰብ ጀመረዋል።

ሌላው አርሶ አደር ሙለታ ገቢሳ በበኩላቸው ጤፍን በመስመር የመዝራትና ስንዴን በቢቢኤም ማረሻ እንዲሁም የተለያዩ የአፈር መዳበሪያ በጠቀም ምርትና ምርታነታቸው እየጨመረ መሆኑን ይገልጻሉ።

በወረዳው የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ ገመቹ ቡልቶ በበኩላቸው በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ምርጥ ዝርያዎችን የማላመድ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዝርያዎቹን ውጤታማነት በማየት ወደ አርሶ አደሩ እንደሚሠራጭም ገልጸዋል።

የጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሽንብራ እና የሌሎች ሰብሎች ምርጥ ዘር ከአየር ንብረቱና ከአካባቢው አፈር ጋር የማላማድ ሥራዎች በማሠልጠኛ ማዕከላቱ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።  

በኩታ ገጠም ማሳ የመዝራትና እርሻውን የማዘመን ስራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማዳረስ እየተሰራ እንደሚገኝም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጣይባ ሀሰን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የሚቀርብለትን የቴክኖሎጂ አማራጭ ተቀብሎ በመተግበሩ ምርታማነቱን እያሳደገ እንደሆነ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ምርታማነቱን በማሳደግ ኑሮውን ከማሻሻል ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያስችለው የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያገኝ ስትራቴጂ ተቀርጾ እንደሚሰራ ወይዘሮ ጣይባ ጠቁመዋል።