በወላይታ ሶዶ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 70 ኩንታል ስኳር ተያዘ

በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 70 ኩንታል ስኳር መያዙን የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ስኳሩ ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር የዋለው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 80610 አዲስ አበባ በሆነ የጭነት መኪና ከከተማው ለመውጣት እየተሰናዳ ባለበት ወቅት መሆኑን በመምሪያው የአስተዳደሩ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ የስራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ሳጅን ፍሬው ሰማ ገልጸዋል።

አሽከርካሪው ለጊዜው በመሰወሩ ስኳሩ ወዴት አቅጣጫ ሊወጣ እንደነበር ማወቅ እንዳልተቻለም አመልክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በከተማው የሚገኝ አንድ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበር ለኅብረተሰቡ ማከፋፈል የነበረበት ሁለት ኩንታል ስኳር ደብቆ በመገኘቱ የወላይታ ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ መረከቡን አስተባባሪው  ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ሕገ-ወጥ ንግድን ከመከላከልና የከተማውን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ከፖሊስ ጋር ተቀናጅተው እያከናወኑት ያሉትን  ተግባር እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል፡፡

ፖሊስ ከስኳር ዝውውሩ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በሶዶ ከተማ የዋዱ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ታደሰ ጋንታ በሰጡት አስተያየት አስተዳደሩ በከተማው የሚስተዋለውን የስኳር እጥረት ለመፍታት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው እርምጃ  ቀጣይነት ሊኖረዉ ይገባል ብለዋል፡፡

በከተማዋ አንድ ኪሎ ግራም ስኳር እስከ 60 ብር ለመግዛት እየተገደዱ ባሉበት ወቅት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመከላከል የተወሰደው እርምጃ እንዳረካቸው የተናገሩት  የጎላ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ከበቡሽ ደመላሽ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከወላይታ ሶዶ ከተማ ወደ ሻሸመኔ መሥመር በተመሳሳይ መንገድ በሕገ ወጥ መንገድ ሊጓዝ የነበረ ሲጓጓዝ የነበረ 20 ኩንታል ስኳር መያዙ ይታወሳል፡፡ (ኢዜአ)