ጃፓን ለትምህርትና ጤና ዘርፎች 452 ሺህ ዶላር ድጋፍ ሰጠች

የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ለትምህርትና ጤና አገልግሎት የሚውል ከ452 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ አደረገ።

የአገሪቱ መንግስት አራት ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለማስፋፋት የሚያስችለውን የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው በኤምባሲው በኩል ነው።   

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ የፕሮጀክት ግንባታና ማስፋፊያ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ፕሮጀክቶቹ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የጉንችሬ እና እነሞር ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታና በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሀሮ ሾጤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ናቸው።   

በተጨማሪም ለሻሻመኔ ከተማ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የምግባረ ሰናይ መጠለያ ግንባታና ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዩሮሎጂ እና ድንገተኛ ክፍል የህክምና መሣሪያዎች ግዥ የሚውል ነው።     

ፕሮጀክቶቹ ከአራት ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አምባሳደር ዲያሱኬ ማሱናጋ እንዳሉት አገራቸው ለኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች።

ጃፓን በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ1989 ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ከ400 በላይ ፕሮጀክቶችን በመሥራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገች ነው።

በትምህርት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በኢኮኖሚ ልማትና ሌሎችም መስኮች ድጋፍ ስታደርግም ቆይታለች።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው የተደረገው ድጋፍ የዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ድጋፉ በተለይም ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መሆኑ የትምህርት ሽፋንን በማስፋት የመንግስትን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡ (ኢዜአ)